Friday, July 10, 2015

ኢትዮጵያ ሚሊዮን ዶላር ለኢንተርኔት ስለላ | ኢትዮጵያ | DW.COM | 09.07.2015

የኢትዮጵያ መንግስት ለስለላ አገልግሎት ከአንድ ሚሊዮን ዶላር ከፍሏል ተባለ። አርቲክል 19 ተብሎ የሚጠራው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ሃኪንግ ቲም ከተባለው ኩባንያ በሚያገኛቸው ግልጋሎቶች የራሱን ዜጎች ይሰልላል ሲሉ የኢትዮጵያን መንግስት ተችተዋል።


Screenshot Hacking Team

0:00:36|0:03:45
«ከፍተኛ ዋጋ ያላቸዉ ታዳኞቻችንን ለማግኘት ችለናል።» ይላል-አቶ ቢኒያም ተወልደ የተባሉ ግለሰብ ሃኪንግ ቲም ለተሰኘ ኩባንያ የጻፉት መልዕክት። መቀመጫውን ኢጣልያ ያደረገው ሃኪንግ ቲም የተሰኘው ኩባንያ ለኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (Information Network Security Agency) የግለሰቦችንና የተቋማትን የመረጃ ልውውጦች፤ዶሴዎች፤ስልክና እንደ ስካይፕ የመሳሰሉ የድምጽና ምስል ንግግሮች መጥለፍ የሚያስችሉ ቁሳቁሶች ሲሸጥ ቆይቷል ተብሏል።
የመልዕክት ልውውጦችንና የመረጃ ሰንዱቅን ሰብረው መግባት የሚችሉ አገልግሎቶችን የሚያቀርበው ይህ ኩባንያ የራሱ ምስጢር ማከማቻ በሌሎች ወገኖች ተሰብሮ፤ በሚስጥር የያዛቸው በቢሮ ውስጥና ከደንበኞች ጋር ያደረጋቸው የመልዕክት ልውውጦችና ዶሴዎች ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለህዝብ ይፋ ሆነዋል።
ይፋ በተደረገው መረጃ መሰረት አብዛኞቹ የድርጅቱ ደንበኞች በሰብዓዊ መብት አያያዝ የሰላ ትችት የሚሰነዘርባቸው አገሮች ናቸው። ከአፍሪቃ፤- ኢትዮጵያ፤ናይጄሪያ፤ሱዳንና ሞሮኮ ይገኙበታል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አርቲክል 19 የፕሮግራሞች ዳይሬክተር የሆኑት ዴቪድ ዲያዝ ኩባንያው ከመንግስታት የስራ ውል እየወሰደ ሲሰራ መቆየቱን ይናገራሉ።
«ኩባንያው መንግስታት ዒላማ ያደረጓቸውን ሰዎች ኮምፒውተሮች ያለ ፈቃዳቸው መመልከት የሚያስችሏቸው ሶፍትዌሮች ያቀርብላቸዋል።ዒላማ የሆኑት ሰዎች ትሮጇያን የተሰኘ የኮምፒውተር ቫይረስ ያለበት መልዕክት ይደርሳቸዋል። መልዕክቱን ሲከፍቱት የመልዕክት ልውውጣቸውን፤ንግግሮቻቸውን እና በኮምፒውተሩ ላይ ያሉ መረጃዎችን አሳልፎ ይሰጣል። የኮምፒውተሩን መቅረጸ-ድምጽና ካሜራ በመጠቀም ዒላማ የተደረጉት ሰዎችን እንቅስቃሴ እና ንግግር መከታተል ያስችላቸዋል።»
ሃኪንግ ቲም የተባለው ኩባንያ ሚስጥር በድረ-ገጽ ላይ ከተዘረገፈ በኋላ ከአቶ ቢኒያም ተወልደ ጋር ያደረጋቸው የመልዕክት ልውውጦች ይፋ ሆነዋል። ድርጅቱ ለኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ላቀረባቸው አገልግሎቶች እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር ክፍያ የጠየቀበት መልዕክት ይገኝበታል። የሃኪንግ ቲም ኩባንያ ደንበኞች የሆኑት አምባገነን መንግስታት እና የደህንነት ተቋማት ትኩረታቸው የተቃዋሚ የፖለቲካ አመራሮችንና ጋዜጠኞችን ማጥመድ መሆኑን ዴቪድ ዲያዝ ተናግረዋል።
«ዒላማ የሚደረጉት ተቃዋሚዎች፤የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፤ጠበቆች፤ሙያቸውን በአግባቡ የሚተገብሩ ጋዜጠኞችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው። ኢትዮጵያ ከኩባንያው ጋር የአንድ ሚሊዮን ዶላር የስራ ውል ነበራት። አሁን ይፋ የሆነው የመረጃ ልውውጥ እንደሚጠቁመው የስራ ውሉ በኩባንያው ላይ ከመገናኛ ብዙሃን የከፋ ትችት ስለተሰነዘረበት ተቋርጦ ነበር። ቢሆንም ትችቱን ችላ በማለት ስልታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለሚታይባት አገር ማቅረቡን ቀጥሏል።»
Symbolbild Multimedia Auge Cyberwar
ባልታወቁ ሰርሳሪዎች በተጋለጠው የሃኪንግ ቲም ምስጢር አቶ ቢኒያም ተወልደ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሞቱ ከስምንት ወራት በኋላ በስማቸው ከተቋቋመው የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ጋር የተገናኙ የድረ-ገጽ አድራሻዎችን መግዛታቸው ይፋ ሆኗል። ይሁንና የድረ-ገጽ አድራሻዎቹ ብቅ ብሎ መጥፋት ቀድሞም ለስለላ እና ብርበራ ተግባር የታቀዱ ሳይሆኑ አይቀሩም እየተባለ ነው።አቶ ቢኒያም ተወልደ ለሃኪንግ ቲም ኩባንያው ለዳንኤል ሚላን በላኩት መልዕክት የገለጹት «ከፍተኛ ዋጋ ያለው ታዳኝ » ማንነት ግን አልታወቀም። ዴቪድ ዲያዝ ሃኪንግ ቲምን የአምባገነኖች ቅጥረኛ ሲሉ ይገልጹታል። አምባገነን መንግስታት ለሚያደርሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ ያደርጉታል።
«በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረግ የመረጃ ልውውጥና ንግግር በሚስጥር የመያዝ መብት ሊከበር ይገባል። እነዚህ ሰዎች ህገ-ወጥ ስራ እየሰሩ ነው የሚል ጥርጣሬ ካለ የሁለቱን ሰዎች የመረጃ ልውውጥ ማየት ይቻላል። ይህ የሚሆነው ግን በዳኛ ብቻ እንጂ በስራ አስፈጻሚዎች አይደለም። የህግ የበላይነት ሊከበር ይገባል።»

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

No comments:

Post a Comment